የዋና ሥራ አስኪያጅ መልዕክት

የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት 2009 ስንቀበል፣ ለመላው የኩባንያው ሠራተኞች መልካም የስራ ዘመን፣ጤናና ደስታ እንዲሆንለት በመመኘትነው፡፡
ያሳለፍነው አመት በፈታኝ ተግዳሮቶች የተሞላ ቢሆንም የነበሩንን ግቦች ከማሳካት አላገዱንም። በተለይም በአብዛኛው የሃገራችን ክፍል ላይ የታየው የኤልኒኖ ክስተት እንኳን ሳይበግረን ኩባንያችን የተቋቋመበትን ልማታዊ አጀንዳ ወደፊት ለማራመድ መቻላችን ትልቅ ውጤት ነው። ኩባንያችን በተለይም በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ለመቋቋም ባደረገው ርብርብ የበኩሉን እገዛ ማድረግ ችሏል፡፡
ኩባንያችን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በሚያስተዳድራቸው የእርሻ ልማቶቹ ከ18,000 ሺህ ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ለመፍጠር ችሏል፡፡ እነዚህም ሰራተኞች ከሚያስተዳድሯቸው ቤተሰባቸው ጋር ወደ 90,000 ኢትዮጵያውያን የኩባንያው ቤተሰቦች ናቸው ያሰኛል፡፡ ይህንንም የስራ እድል ፈጠራ በአዲሱ ዓመትም አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡
የስመዘገብነውን የእድገት ጎዳና ወደ አዲሱ 2009 ዓ.ም. በስኬት ለማሸጋገርና ዘለቄታዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ያስችለን ዘንድ ኩባንያችን አራት መሰረታዊ መርሆዎች ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ- የተሻሻለ አስተዳደርና ስርዓት እንዲኖር፡-
የኩባንያው ኃላፊዎች በተቀናጀ መልኩ የኩባንያውን ዓላማዎች ለማሳከት መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ጥብቅ ወጪ ቁጥጥር እና ምርታማነት ማሳደግ ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፡፡
ኩባንያው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ስራዎች ለማሳካት ሁሉም የስራ ክፍሎች በጋራና ለአንድ ዓላማ በመቆም ዘለቄታዊነቱን ለማረጋገጥ በጋራ የመስራትን ባህል የበለጠ ማጎልበት አስፈላጊ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ፡- አዳዲስ የስራ ዕድሎችን የማሳዳግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በሀገር ውስጥ ስትራቴጂክ የኢንቨስትመንት እድሎችን መለየትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለንን ግንኙነት የማጠናከርና አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ፈልጎ በማፈላለግ ኩባንያችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል፡፡
በሶስተኛደረጃ፡- የኢትዮ አግሪ-ሴፍት እርሻዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን ትብብር አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ በተለይም በኩባንያው ሠራተኞች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የመንግስት አካላት እና ከንግድ አጋሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት በቀናነትና በባለቤትነት ስሜት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ተረባርበን መስራት ይኖርብናል፡፡
በመጨረሻም ለማሳሰብ የምፈልገው የተለያዩ ተግዳሮቶችና በተለይም የላ-ኒና የአየር ስርጭት በ2009 ዓ.ም. ይጠበቃል፡፡ እነዚህን ተቋቁመን ባለፈው ዓመት ያስመዘገብነውን ትርፋማነት ለመድገም ጠንክረን መስራት ይኖርብናል፡፡
በአዲሱ ዓመት ያቀድናቸውን ተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የምንጀምርበት ጊዜ በመሆኑ በቁርጠኝነት ተጠናክረን ከሰራን እውንእንደምናደርገው አልጠራጠርም፡፡
አመሰግናለሁ!